2 ሰኑስረት
==
2 ሰኑስረት | |
---|---|
የኻይከፐሬ ምስል | |
የግብጽ ፈርዖን | |
ግዛት | 1905-1888 ዓክልበ.? |
ቀዳሚ | 2 አመነምሃት |
ተከታይ | 3 ሰኑስረት |
ሥርወ-መንግሥት | 12ኛው ሥርወ መንግሥት |
አባት | 2 አመነምሃት |
==
ኻይከፐሬ፣ ፪ ሰኑስረት ግብጽን በመካከለኛ መንግሥት (12ኛው ሥርወ መንግሥት) ከ1905 እስከ ምናልባት 1888 ዓክልበ. ግድም ድረስ የገዛ ፈርዖን ነበረ። የአባቱ 2 አመነምሃት ተከታይ ነበር። በተለይ የሚታወቀው በኤል-ላሑን ስላሠራው ሀረም ነው።
በኑብካውሬ ፪ አመነምሃት ዘመነ መንግሥት በ፴፫ኛው ዓመት (1907 ዓክልበ. ግድም) ልጁን 2 ሰኑስረት ከእርሱ ጋር በጋርዮሽ ወደ ዙፋኑ አስነሣው። ከዚህ ሁለት ዓመት በኋላ በ1905 ዓክልበ. ግድም ኑብካውሬ ዓረፈና ፪ ሰኑስረት ለብቻው ፈርዖን ሆነ ይመስላል።
በጠቅላላ ስንት ዓመታት ያሕል እንደ ነገሠ ተከራካሪ ነው። ማኔጦን ለኻይከፐሬ ፪ ሰኑስረት እና ለተከታዩ 3 ሰኑስረት ፈንታ ለሁለቱ አንድ ስም ብቻ አለው፤ እሱም ሴሶስትሪስ ሲሆን ለ፵፰ ዓመታት እንደ ገዛ ይለናል። ይሄ ሴሶስትሪስ እስከ እስኩቴስ ድረስ የዘመተ በአፈ ታሪክ ይባላል። ፫ ሰኑስረት ቢያንስ በከነዓን እንደ ዘመተ ይታወቃል፤ ለ፪ ሰኑስረት ግን ምንም ዘመቻ አይታወቅም።
የቶሪኖ ቀኖና የሚባለው የፈርዖኖች ዝርዝር ሰነድ ሁለቱንም ይለያል፤ ለ፪ ሰኑስረት ፲፱ ዓመታትና ለ3 ሰኑስረት ፴ አመታት ይሠጣል። ነገር ግን ለ፪ ሰኑስረት ከ፰ኛው ዓመቱ በላይ የሆነ ዓመት ቁጥር በሥነ ቅርስ ስለማይታወቅ፤ ብዙ መምህሮች ለ፰፣ ፱ ወይም ፲ ዓመታት ብቻ እንደ ነገሠ ያምናሉ።
መጀመርያ ፫ቱ ዓመቶቹ ከአባቱ ፪ አመነምሃት በጋርዮሽ ሲሆኑ፣ ከዚህ በላይ ልጁን 3 ሰኑስረት በጋርዮሽ ወደ ዙፋኑ እንዳስነሣው የሚመለከት ማስረጃ አለ። ከዚህ ውስጥ አንድ የፓፒሩስ ሰነድ ሁለቱን ፈርዖኖች ሲጠቅስ በ፪ ሰኑስረት ፲፱ኛው ዓመትና በ፫ ሱኑስረት ፩ኛው ዓመት እንዳለ ይታስብ ነበር። ሆኖም ሌሎች መምህሮች በተቃራኒው በ፫ሰኑስረት ፲፱ኛው ዓመትና በተከታዩ በ3 አመነምሃት 1ኛው ዓመት እንደሚለው ያምናሉ።
በዩጂን ሜሪል አስተሳሰብ፣ ይህ ፈርዖን ዮሴፍን የሾመው በኦሪት ዘፍጥረት ፵፩ ዘንድ ይሆናል። ይህም ደግሞ በመጽሐፈ ኩፋሌ ካለው አቆጣጠር (2164 ዓ.ዓ. ወይም 1907 ዓመት ከክርስቶስ ልደት በፊት ግድም) ጋር ይስማማል። በዚህ ሥርወ መንግሥት የሌሎቹ ፈርዖኖች ጠቅላይ ሚንስትሮች ሁሉ በስም ቢታወቁ፣ የዚህ ፪ ሰኑስረት ሚኒስትር ስም ግን ከቶ አልታተምም፤ በዘፍጥረትም የዮሴፍ ግብጽኛ ስም «ጸፍናት ፐዕናህ» ሆነ።
ቀዳሚው 2 አመነምሃት |
የግብፅ ፈርዖን | ተከታይ 3 ሰኑስረት |
-
የኻይከፐሬ ሀረም በኤል-ላሑን
-
በኻይከፐሬ ሴት ልጅ መቃብር የተገኘው ድሪ
-
«ኻይከፐሬ» የሚል ካርቱሽ